ስለኛ

ስለኛ አጠር ያለ መረጃ

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቃለ ዐዋዲ ምዕራፍ ስድስት፣ ዐንቀጽ ሠላሳ ስምንት እስከ አርባ አምስት ድረስ በተዘረዘረው መሠረት ከጠቅላይ ቤተ ክህነት ጠቅላይ ጽ/ቤት ቀጥሎ በቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅር መሠረት የመንበረ ጵጵስና ሀገረ ስብከት መሥርቶ እና አጠናክሮ መሥራቱ ለቤተ ክርስቲያን አንድነት አስፈላጊ እና ወሳኝ ነው፡፡ በቃለ ዐዋዲው ዐንቀጽ አርባ ሦስት ቁጥር አንድ ላይ እንደ ተገለጠው «የመንበረ ጵጵስና ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት በሀገረ ስብከቱ ክልል ውስጥ ለሚገኙ ገዳማት፣ አድባራት እና የገጠር አብያተ ክርስቲያናት እንዲሁም በየደረጃው ለተቋቋሙት ሰበካ መንፈሳውያን ጉባኤያትና ለወረዳ ቤተ ክህነት የሥራ አመራርና ከፍተኛ የአስተዳደር ኃላፊነት ያለው መሥሪያ ቤት ነው» በእንግሊዝኛው «ዳዮሰስ» የሚለው ቃል dioikesis ከሚለው የግሪክ ቃል የመጣ ነው፡፡ በመሆኑም ሀገረ ስብከት ማለት በአንድ ሊቀ ጳጳስ የሚመራ አንድ አካባቢ ማለት ነው፡፡ ሀገረ ስብከት ለመጀመርያ ጊዜ በሥራ ላይ የዋለው ቅዱሳን ሐዋርያት የጌታችንን ትምህርት ተግባራዊ ለማድረግ ዓለምን ዕጣ በዕጣ ተከፋፍለው ለማስተማር በወጡ ጊዜ ነው፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያት ይመቻል፣ አይመችም ሳይሉ በተሠማሩበት ሀገረ ስብከት ገብተው አብያተ ክርስቲያናትን በመትከል፣ ምእመናንን አስተምረው በማጥመቅ፣ ካህናትን እና ዲያቆናትን በመሾም የወንጌልን ቃል ለዓለም አዳርሰዋል፡፡ ቅዱስ ጴጥሮስ በሮም ሀገረ ስብከቱ፣ ዮሐንስ ወንጌላዊው በታናሽ እስያ ሀገረ ስብከቱ፣ ቶማስ በሕንድ ሀገረ ስብከቱ፣ማርቆስም በእስክንድርያ የሠሩት ሥራ ለዚህ ማስረጃችን ነው፡፡

የአዲስ አበባ ሀገረስብከት ቀጠሮ ማስያዣ ምንነት

የፕሮጀክቱ አላማ እና ፍላጎት ለመጠቀም ቀላል፤ ደንበኞች በቀላሉ ቀጠሮ ማስያዝ እና በቀጠሮ ሰዓታቸው ብቻ የሚስተናገዱብት ስርአት ማብልጸግ ነው። ስርአቱ የኢትዮጲያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት አባላቶች/ባለጉዳዮች ቀጠሮዎችን የሚቆጣጠር እና ቀጠሮዎችን የሚመዘግብ ሆኖ እነዚህን በአንድ ገጽ ላይ ጠቅለል ያለ ዝርዝር እና ሰፋ ያለ ሪፖርት ማየት እንዲያስችል ተደርጎ የሚሰራ ድህረገጽ መሰረት ያረገ የዴስክቶፕ መተግበሪያ ይሆናል።

የቀጠሮ አስተዳደር ስርዓት ጥቅሞች
✓ የሰራተኞችን ግዜ ብክነት ይቀንሳል
✓ ሁሉም ባለጉዳይ የሚስተናገደው በቀጠሮ ብቻ ነው
✓ የባለጉዳዮች ጭንቀትን እና እንግልት ይቀንሳል (ባለጉዳዮች በቀላሉ ካሉበት ሆነው ጉዳያቸውን መከታተል ይችላሉ)
✓ በሃገረስብከቱ አካባቢ የሚከሰተውን የባለጉዳዮች ወረፋ እና መጨናነቅ ያስወግዳል   
✓ በተግባር ውስጥ የጊዜ መዘግየትን ይቀንሳል
✓ ተደጋጋሚ የባለጉዳዮች ማመልከቻ እና እልባት በቀላሉ ለመከታተል እና ድግግሞሽን ያስወግዳል